ድሬዳዋ፡— በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙ ሕፃናትን ከረሃብና ከተመጣጠነ ምግብ እጥረት በመታደግ፣ ዕውቀትንና ጤናን የተላበሰ አገር ተረካቢ ትውልድ ለመቅረጽ ያለመ ታሪካዊ የልማት ፕሮጀክት በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በይፋ ተመረቀ። ማዕከላዊ የማብሰያ ቤት (Central Kitchen)፣ ዘመናዊ የሕፃናት መመገቢያ እርሻ (Smart Farm) እና የሕግ ማዕቀፍን በአንድነት ያካተተው ይህ ፕሮጀክት፣ በኢትዮጵያ የትምህርት ቤቶች ምገባ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተና ለሌሎች ክልሎችም አርአያ የሚሆን ተሞክሮ ያበረከተ ሆኗል።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች፣ የልማት አጋሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ይፋ የሆነው ይህ ስራ፣ የከተማ አስተዳደሩ በትውልድ ግንባታ ላይ ያስቀመጠው ዘላቂ አሻራ ተደርጎ ተወስዷል።
ቁርጠኝነት፣ ትብብርና የባለሀብቱ ሚና
የኢትዮጵያ የትምህርት ቤቶች ምገባ ኢኒሼቲቭ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ክብርት ወ/ሮ ፍሬዓለም ሽባባው በምረቃው ወቅት እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ እውን ሊሆን የቻለው በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች አርቆ አሳቢነትና ፈጣን ውሳኔ ሰጪነት ነው። ከከንቲባው ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር ያለው አመራር ፕሮጀክቱ ለትውልድ ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ፣ በአንድ መንፈስና በቡድን በመንቀሳቀስ ለሥራው መሳካት ግንባር ቀደም ድርሻ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።

“በዚህ ከተማ ውስጥ አንድም ልጅ እንዳይራብ የወሰዳችሁት እርምጃና የሰጣችሁት ፈጣን ምላሽ ለሀገራችን ትልቅ ምሳሌ የሚሆን ነው” ወ/ሮ ፍሬዓለም ሽባባው በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ ተናግረዋል።
ይህንን ቅዱስ አገራዊ ዓላማ ከመነሻው ጀምሮ በቅርበት በመከታተል፣ ሀብትና ጉልበትን በማስተባበር ረገድ ወጣቱ ባለሀብት ቤጃይ ኒከር (Bejai Nicker) ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ ከወረቀት አልፎ መሬት እንዲይዝ ላደረገው ላቅ ያለ ተሳትፎ ምስጋና ቀርቦለታል። በተጨማሪም የኢኒሼቲቩን ጉዞ ከመጀመሪያው ጀምሮ በገንዘብ፣ በዕውቀትና በቁሳቁስ በመደገፍ ለስኬት ያበቁትን የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF Ethiopia) አመራሮችና ባለሙያዎችን ወ/ሮ ፍሬዓለም አግልግሎታቸውን ከፍ ብሎ ይዘከራል ሲሉ ገልጸዋል።
የአየር ንብረት ተስማሚ ቴክኖሎጂና ዘላቂነት
ይህ በድሬዳዋ የተመሰረተው ዘመናዊ የምግብ ሥነ-ሥርዓትና ስማርት እርሻ፣ የአካባቢ ብከላን በሚቀንስና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በሚስማማ (Climate-Smart) ቴክኖሎጂ የተገነባ ነው። የፕሮጀክቱ ልዩ ባህሪ ከምግብ ማብሰያ ሂደቱ የሚወጡ ተረፈ ምርቶች መሬት ላይ እንዳይጣሉ በማድረግ፣ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውሉና ለእርሻ የሚሆን ኮምፖስት (ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ) እንዲሆኑ ተደርጎ የተቀረጸ መሆኑ ነው።

የፕሮጀክቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በበላይነት ለመከታተልና ለመምራት “የድሬዳዋ ስኩል ፊዲንግ ኤጀንሲ”የተባለ ተቋም የተመሰረተ ሲሆን፣ ተቋሙ በምረቃው ዕለት ሥራውን በይፋ ተረክቧል።

ከተማ አስተዳደሩ የሥራውን ቀጣይነት በግለሰቦች በጎ ፈቃድ ላይ ብቻ እንዳይመሰረት ለማድረግ፣ ጠንካራ መዋቅራዊ የሕግ ማዕቀፍ አዘጋጅቷል። ፕሮጀክቱ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የውስጥ አቅም የሚደገፍ እንዲሆን ከሚለው መርህ በመነሳት፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከከተማዋ በታክስ ከሚገኝ ገቢ ላይ ለምገባ ፕሮግራሙ ቋሚ የፋይናንስ ድጋፍ (ድጎማ) ለማድረግ መወሰኑ በዕለቱ ትልቅ እመርታ ተብሎ ተወድሷል።
የወደፊት ራዕይና የክህሎት ልማት
የምገባ ፕሮግራሙ የሕፃናትን የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት በማረጋገጥ የትምህርት ጥራትንና የመማር አቅምን ከማሳደግ ባለፈ፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድልና የዕውቀት ሽግግር የሚፈጥር መሆኑ ታውቋል።
የኢኒሼቲቩ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ፍሬዓለም ሽባባው ለሆርን ኒውስ ሃብ (Horn News Hub) በስልክ እንደገለጹት፣ ተቋሙ ከምገባው ጎን ለጎን የወደፊት ሕይወታቸውን ከግብርና ሥራ ጋር ማቆራኘት የሚፈልጉ ወጣቶችን ያበቃል፡

#የታለመው የዕድሜ ክልል፦ ከ11ኛ ክፍል እስከ ኮሌጅ ያሉ 50 ወጣቶች በመጀመሪያው ዙር ይመለመላሉ።
#የሥልጠናው ይዘት፦ ለአንድ ዓመት የሚቆይ የተግባርና የንድፈ-ሐሳብ የክህሎት ሥልጠና ይሰጣል።
#ዓላማው፦ወጣቶቹ በዘመናዊ ግብርናና ስማርት እርሻ ላይ የሰለጠነ የሰው ኃይል ሆነው እንዲመረቁና ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ነው።

ይህ በድሬዳዋ የተዘረጋው የተቀናጀ ሥርዓት፣ ረሃብን ከትምህርት ገበታ ላይ ከማጥፋት ባለፈ፣ የአየር ንብረትን የጠበቀ የከተማ ግብርና እና ዘላቂ የሕግና የፋይናንስ መዋቅር በአንድ ላይ እንዴት መጓዝ እንደሚችሉ ለቀሪው የኢትዮጵያ ክፍሎች አዲስ መነሳሳትን የፈጠረ ሞዴል ሆኗል።






